የግማሽ ዓመት ሥራ አፈጻጸም በመገምገም የአመቱ እቅድ ለማሳካት የድርጊት መርሀግብር ተዘጋጅቷል
ቪዥንፈንድ ማይክሮፋይናንስ አ.ማ የግ ማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሁሉም የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች በተገኙበት ለ2 ተከታታይ ቀናት ከጥር 6-7/2014 ዓ.ም ተገምግሟል፡፡ ሁሉም ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ከእቅድ አንጻር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በግማሽ አመቱ የቁጠባ መጠንና የብድር አቅርቦት ጨምሯል፤ ብድር የማስመለስ ሥራና ተቋሙ ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ የፋይናንስ አቅርቦትና ተደራሽነት ምጣኔ ላይ ለውጥ ታይቷል፡፡ የተበዳሪዎችና ቆጣቢዎች ቁጥር ለመጨመር በተሰራው ሥራ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አበረታች መሆኑ ተገምግሟል፡፡ የተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ልቀት ብሎም የሠራተኛ የአቅም ግንባታ ላይ የተሰራ ሥራ መሻሻል ማሳየቱ በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በፋይናንሽያል ኢንዱስትሪ ውሰጥ ተፎካካሪና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት አገልግሎታችን ማዘመንና ፈጣን፤ ቀልጣፋ ብሎም ተደራሽ ማድረግ አለብን ብለዋል የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታዬ
ጭምዴሳ፡፡ አክለውም የቁጠባና የብድር ሥርጭት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፤ በሁሉም መስፈርት የአፈጻጸም ጥራት ለማምጣት አቅም ያላቸው ሠራተኞች ተቋሙን እንዲቀላቀሉ ትኩረት
ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡
ሁሉም ቅርንጫፎች በኮር ባንኪንግ ለማገናኘት አመርቂ ሥራ የተሰራ ቢሆንም በኢንተርኔት መቆራረጥ ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት መፈጠሩ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በየአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ፤ በአፈጻጸም ክፍተት ላይ ጉልህ ሚና እንደነበረው ሁሉም ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ከእቅድ አንጻር የተሰሩ ሥራዎች ቢኖሩም አመታዊውን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት ተመላክቷል ፡፡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነትና በሌሎች አካባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ የቅርንጫፎቹ ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሯል ተብሏል፡፡ በግማሽ አመት ግምገማ መሰረት የተሻለ አፈጻጸም ያመጡ የአካባቢ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የምዕራብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የ1ኛ ደረጃ ቦታን ሲያገኝ የማዕከላዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት 2ኛ እና ሰሜን ምእራብ ደግሞ 3ኛ ደረጃን በማግኘት የግማሽ
አመት የሥራ አፈጻጸምን በላቀ ሁኔታ አጠናቋል፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች በስራቸው የሚገኙ ቅርንጫፎችን በመከታተል በመደገፍና ፈጣን ግብረ መልስ በመስጠት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው አቅጣጫ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታዬ የብድር ሥርጭትና ማስመለስ ሥራ ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ጥንቃቄ በተሞላበት እንዲከናወን አሳስበዋል፡፡