'የዳኝነት ስነ-ምግባር' ወርክሾፕ በሀዋሳ ከተማ ተካሄደ

ቪዥንፈንድ ማይክሮፋይናንስ አ.ማ ከፌዴራል የፍትህ እና የህግ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ከሲዳማና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተወጣጡ ዳኞች የተሳተፉበት የ’ዳኝነት ስነ-ምግባር’ ወርክሾፕ በሀዋሳ ከተማ ታህሳስ 16/2014 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

አቶ ሰለሞን ወ/ጊዮርጊስ የቪዥንፈንድ ማይክሮፋይናንስ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ (ሰፖርት ሰርቪስ ዘርፍ) የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ወርክሾፑን ያስጀመሩት ሲሆን በንግግራቸውም ቪዥንፈንድ ሁለንተናዊ የሆነ ለውጥ ለማምጣት ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ከባለደርሻ አካላት ጋር በአጋርነትና በትብብር መስራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡  

በተጨማሪም ተቋሙ የደረሰበትን አጠቃላይ የአገልግሎት ደረጃ ለተሳታፊዎች ያቀረቡት አቶ ሀይሉ ለታ የቪዥንፈንድ ማይክሮፋይናንስ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ (የኦፕሬሽን ዘርፍ) ሲሆኑ ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አማራጭ ያላቸውን የቁጠባና ብድር አገልገሎት ለበርካታ ኅብረተሰብ ክፍል በማቅረብ በድህነት ቅነሳ ውስጥ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

ቪዥንፈንድ ማይክሮፋይናንስ ከፌዴራል የፍትህ እና የህግ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የ’ዳኝነት ስነ-ምግባር’ ወርክሾፕ በማዘጋጀት በክልሎቹ ለሚገኙ ዳኞች እንዲሰጥ ማድረጉ እጅግ የሚበረታታና ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው መሰል ሥልጠናዎች የዳኝነት ኢ-ፍትሃዊነት ችግሮችን በመቅረፍ ማኅበረሰቡ ቀልጣፋና ፍትሃዊ የዳኝነት አገልግሎት እንድያገኙ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል የክቡር እንግዳ አቶ ኤርሲኖ አቡሬ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት፡፡

ከፌዴራል የፍትህ እና የህግ ኢንስቲትዩት የመጡ ባለሙያዎች የዳኝነት ስነ-ምግባር በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ  ቅባሎትን ያገኙና በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የዳኝነት ስነ-ምግባርና ሌሎች ተዛማጅ ርዕሰ-ጉዳዮችን ለተሳታፊዎች ያቀረቡ ሲሆን በተነሱ ጉዳዮች ላይም ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ሰልጣኞቹም ባገኙት ግንዛቤ መደሰታቸውን ተናግሯል፡፡ ቪዥንፈንድ ማይክሮፋይናንስ አ.ማ ሰርቶ ለመለወጥ ፍላጎት ያላቸው ነገር ግን በገንዘብ እጥረት ለሚቸገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቁጠባና ብድር አገልግሎት በማቅረብ እንደ ክልሉ ከፍተኛ አስተዋጽዎና ሚና እየተወጣ የሚገኝ ተቋም እንደመሆኑ መጠን፤ ከሥራው ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙትን የትኛውም የዳኝነትና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል ተሳታፊዎቹ፡፡

ወርክሾፑ በዚህ ደረጃ እንዲዘጋጅ ሲያስተባብር የነበረው የሕግ አገልግሎት ክፍል ሲሆን ወርክሾፑ በዚህ ደረጃ መዘጋጀት በተቋሙና በክልሎቹ መካከል ቀጣይ ሥራዎችን በጋራ ለመስራት የጎላ ሚና እንዳለው የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ክፍሌ ገልጸዋል፡፡